የመተማመን መትነን በኢትዮጵያ
ገለታው ዘለቀ
በመጀመሪያ ደረጃ መተማመን (Trust) ስንል የአንድ ሕብረተሰብ የጋራ ሀብት ወይም የማኅበራዊ ካፒታል ዋና አካል መሆኑን እናንሳ። በአጠቃላይ ማኅበራዊ ካፒታል ስንል ደግሞ ልክ እንደሌሎቹ የሰው ልጆች ካፒታል የሚታይ ነው። ለምሳሌ የገንዘብ ካፒታል፣ የሰው ካፒታል (Human capital) እንደምንለው ማኅበራዊ ካፒታልም ካፒታል ይባላል። ካፒታል ነው እንደንል የሚያስችለን ምክንያት አንድም ልክ እንደሌሎቹ ካፒታሎች የሚመረት (Produce የሚደረግ) መሆኑና ለተለያዩ የማኅበረሰብ ልማቶች ኢንቨስት የምናደርገው ሀብት በመሆኑ ነው። እነዚህ ተፈጥሮዎቹ ከሌሎች ካፒታሎቻችን ጋር ያመሳስሉታል።
የሰው ልጅ የሚያመርተውና ለተለያየ ልማቱ የሚጠቀምበት ይህ ማኅበራዊ ካፒታል ልክ ሌሎች ሀብቶችን ለማምረት አቅደን እንደምንሰራው ተጠንቅቀን ልናሳድገውና ልንይዘው በአስፈላጊው ቦታና ጊዜ ሁሉ በኢንቨስትመንት ላይ ልናውለው የሚገባ ትልቅ ሀብት ነው። አዳም ስሚዝ የተባለው እውቁ የምጣኔ ሀብት ተጠባቢ በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ አንድ የማይታይ እጅ (Invisible hand) አለ እንደሚለው የማኅበራዊ ሀብት ዋና አካል የሆነው መተማመን በሰው ልጆች እድገት ውስጥ አንዱ የማይታይ እጅ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው። በጠቅላላው ማኅበራዊ ካፒታል ሕብረተሰብ የሚያመርተውና ለሕይወቱ የሚጠቀምበትም ነው ብለናል። ታዲያ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ማኅበረሰቡ ራሱ የሚፈጥራቸው ሦስት ዓይነት ማኅበራዊ ካፒታሎች እንዳሉ የማኅበራዊ ካፒታል አጥኒዎች ይነገራሉ። አንደኛው አዎንታዊ ማኅበራዊ ካፒታል ሲሆን፤ ሁለተኛው አሉታዊ ማኅበራዊ ካፒታል ይባላል። ሦስተኛ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ገለልተኛ ማኅበራዊ ካፒታል (Neutral Social Capital) ሊሆን ይችላል።
አዎንታዊ ማኅበራዊ ካፒታል (Positive social capital) የሚባሉት ከሕብረተሰቡ ባህል፣ ወግ ልማድ፣ ኃይማኖት አካባቢ የሚመነጩ ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ እድገት አስተዋጾ ያላቸው ሀብቶች ናቸው። ለምሳሌ ስራን የሚያበረታቱ ስነቃሎች፣ እርስ በርስ መተማመን፣ የፍቅር ሀብት፣ ታማኝነት፣ ምክንያታዊ የሆነ የቁጠባ ባህል፣ የመረዳዳት ባህል ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው። በአንጻሩ አሉታዊ (negative social capital) የሚባሉት ደግሞ አንድ ሕብረተሰብ በግልጽም ይሁን በህቡዕ እየተለማመዳቸው ያሉ ነገር ግን ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ እድገት አደናቃፊ የሆኑ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ብናነሳ አንዳንድ አደገኛ ባህሎችን መጥቀስ እንችላለን። ስራን የማያበረታቱ ስነ ቃሎች፣ ሃሜት፣ የጫት ባህል፣ ሌሎች በባህሎቻችን ውስጥ ያሉ እንደ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ግግ ማውጣት፣ እንጠል መቁረጥ፣ ሰውነትን በስለት መተልተል፣ ከባህል ጋር ተያይዞ በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸሙ በደሎች፣ በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ባህላዊ ግድፈቶች ወዘተ. ሕብረተሰብ የፈጠራቸው ነገር ግን ለሕብረተሰብ እድገትና ምርታማነት ኢንቨስት ሊደረጉ የማይችሉ እንዴውም ጎታችና አደናቃፊ ናቸውና አሉታዊ ማኅበራዊ ካፒታል ሊባሉ ይችላሉ። አፍሪካ ውስጥ ተቆጥሮ የማያልቅ አሉታዊ ካፒታል ያለ ሲሆን ይህንን ለመቀነስ ትልቅ ዘመቻ ያስፈልጋል። አለበለዚያ የሰባዊ እድገትን ከፍ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ቶሎ ግቡን አይመታም። ሌላው ካፒታል ገለልተኛ የሚባለው ሲሆን ይሄ በሰው ልጆች ሁሉንተናዊ እድገት ላይ የጎላ አሉታዊ ተጽእኖ የሌለው ሊሆን ይችላል። እንዲህ አይነቶቹን ለጊዜው ችላ ብሎ አሉታዊ ካፒታሎችን የመቀነስ አዎንታዊ ካፒታሎችን የማሳደግ ስራ ያስፈልጋል።
ለመግቢያ ስለ ማኅበራዊ ካፒታል ይችን ያክል ዳራ ከሰጠን ከማኅበራዊ ካፒታል ውስጥ አንዱ ዋና ነገር መተማመን ነው። በዚህ ዙሪያ ጥቂት ውይይት እናድርግ። መነሻችንም ይሄው ነውና። ማኅበራዊ ካፒታል ስንል፣ መተማመንን፣ የሕብረተሰብ ኔትወርክን (Networks)፣ ለጋራ ጥቅም በጋራ ለመስራት መስማማት፣ መደጋገፍ (Reciprocity) ፣ ልማዶች (norms) የሚመለከት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ መተማመንን (Trust) ብቻ መዝዘን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ብንገመግም ጥሩ መስሎኛል።
በኢትዮጵያ ሁኔታ የመተማመን ሀብታችንን በሦስት ሀገራዊ የመተማመን የፍስሰት አቅጣጫዎች መገምገም እንችላለን። እነዘህ ሦስት የመተማመን መፍሰሻዎች፤
1. የግለሰብ መተማመን (Interpersonal trust)
2. ቀጥታ መተማመን (Vertical trust)
3. የጎኖሽ የቡድን መተማመን(Cross cultural interpersonal trust)
ናቸው።
ጦሽ ነው የሚታየው። ሌሎች ጥናቶችን ብናገላብጥ ለምሳሌ ያህል የዓለም የብልጽግና ደረጃ መለኪያ (Legatum prosperity Index) የሚያወጣውን ጥናት ብናይ ኢትዮጵያዉያን በፍትህ ላይ በጣም ዝቅተኛ መታመን (Very low confidence) ነው
ያላቸው ይላል። በአንድ ሀገር ውስጥ በተለይም ዋና ዋና በተባሉት ተቋማት ላይ ማለትም፣ በፍርድ ቤት፣ በሲቪል ሰርቪስ፣ በፖሊስ፣ በወታደሩ፣ ሚዲያው ላይ እምነቱ ከተነነ ያ ሀገር በኢኮኖሚም ሆነ በሰባዊ ልማት ወደፊት መራመድ አይችልም። ይህንን ዝቅተኛ ማኅበራዊ ካፒታል ይዞ በጥንድ እያደግን ነው ማለት አይቻልም።
የመታመን መትነን በመንግሥትና በህዝብ መካከል ሲከሰት ተቃውሞዎች ይበዛሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በዚህ መንግሥት ጊዜ በስፋት የሚታየው ተቃውሞም በመንግሥት ላይ ከፍተኛ እምነትን ከማጣት የመጣ ነው። ባለፈው ጊዜ እንደተወያየነው አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ያለማልኛል ብሎ ሳይሆን በተቃራኒው አጥፊ ነው ብሎ ካመነ ያ ሥርዓት ባስቸኳይ መለወጥ አለበት። የተነነን መታመን በቀላሉ ማዝነብ አይቻልም። የግድ ለውጦች መምጣት ይጠበቅባቸዋል። አንዳንዴ ከህዝቡ መሃል ስለሚዲያ የሚነገር ነገር አለ። ሚዲያውን ያለማመን፣ ለመንግሥት ብቻ መሳሪያ መሆኑን ማመን፣ በመንግሥትና በህዝብ መካከል መተማመንን ያተነነ አንዱ ጉዳይ ነው። የመንግሥት በፍርድ ሂደት ውስጥ ጣልቃ መግባት በከፍተኛ ሁኔታ መተማመንን የሚያተን ተግባር ነው። በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ በሚያሰሙ ዜጎች ላይ መትረየስና ከባድ መሳሪያ የታጠቀ ወታደር ማሰማራት በመንግሥትና በህዝብ መካከል መታመንን እያተነነ አምባገነናዊ ከባቢን የሚፈጥር ነገር ነው። የሲቪል ሰርቪሱ ሴክተር እድገት የሚሰጠው፣ የሚቀጥረው በፖለቲካ ታማኝነት መሆኑን ህዝብ ሲደርስበት መተማመን ይተናል። እንዲህ መተማመን የተነነበት ሀገር በአምስት ዓመት ትራንስፎርሜሽን እቅድ እናሻሽለዋለን ማለት ሌላ የቀረች ጥቂት እምነት ካለች እሷኑ ጨርሶ ለማትነን ነው። ቀጥታ መታመንን ከሚያሳዮ ሌሎች አንጻራዊ ጥናቶች ስናይ ለምሳሌ ፍሪደም ሃውስ የሚያወጣቸውን ጥናቶች በየጊዜው ስናይ ኢትዮጵያ ነጻ ያልሆነች ሀገር ናት። መንግሥትና ህዝብ የሚደባበቁባት፣ የሚጠራጠሩባት ሀገር ናት። ይህ አይነት መንግሥት በተለይ ብዙ ብሔሮች ያሉበትን ሀገር ሲመራ አደጋው ዘርፈ ብዙ ነው። ግጭቶች እንደ ጭስ ቀዳዳ እየፈለጉ ሲወጡ አንዳንዴ በብሔር በኩል እየፈነዱ ብሔራዊ ማንነትን እየሸረሸረ ይመጣል። የዚህን የቀጥታ መታመን ሀብታችንን ስናጤን በህዝብና መንግሥት መሃል እንዲህ መታመን ተንኖ እንዴት ነው የምንኖረው? የሚል አስገራሚ ነገር ይነሳል። በርግጥ ያው አንድ አምባገነን ሥርዓት በኃይል ያስተዳድራል። ነገር ግን ከዓመታቶች በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ሰው ይለው የነበረው ነገር ትዝ አለኝ። እኛ መንግሥት የለንም ይል ነበር ህዝቡ። የምንኖረው በቤተሰብ ሕግና በባህላዊ ተቋማት ነው ይሉ ነበር። መንግሥት ስወለድም ስሞትም አያውቀኝም፣ ግብር ለመሰብሰብ ብቻ ብቅ ይላል የሚሉ ወገኖች ብዙ ናቸው። እነዚህ ወገኖች የውነትም በባህላዊ ተቋሞቻቸውና በቤተሰብ ህጎች ነው ብዙውን ሕይወታቸውን የሚገፉት እንጂ ከመንግሥት ጋር ያላቸው መስተጋብር እጅግ ቀጭን ነው። የማኅበራዊ ዋስተና ቁጥር እንኳን የለንም።
በርግጥም ለአንድ ሀገር የዜጎች የእርስ በርስ መታመን መኖር ሀገርን ለመጠበቅ ይጠቅማል። ትልቁ ሀብትም ይህ ነውና መጠበቅ አለብን። መንግሥት ዘላቂ አይደለም። መንግሥት ሲቀየር ያ የተነነው መታመናችን ይመለሳል፣ ይዘንባል። ነገር ግን በዜጎች መካከል መታመን ሲጠፋ እሱ የበለጠ አደገኛ ነው። በቀላሉ አናመርተውም እንደ ሌሎች የፋብሪካ ምርቶቻችን በቀላሉ የምናመርተው ካፒታል አይደለምና። መታመናችንን ለማደስ ብዙ ጊዜ ይፈጅብናልና።
ወደ ሦስተኛው የመታመን አቅጣጫ እናምራ። በእኛ ሀገር ሁኔታ የመታመን ካፒታላችን በብሔር ዘለል ደረጃም መጠናት አለበት። አንድ የብሔር አባል ከሌላው ጋር ሲገናኝ በምን ያህል የመተማመን ደረጃ ይኖራል የሚለውን ማጥናት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን እንድናደርግ የሚያስገድደን ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የብሔር ፌደራሊዝም ከግምት በማስገባት ነው። የብሔር ፖለቲካ በሰለጠነበት ሀገር ተዋረዳዊ የመታመንን ካፒታል ደረጃ ማጥናትና ደረጃውን እያዩ በተለያዩ ዘዴዎች ይህን ካፒታል ለማሳደግ መሞከር ለሀገር አንድነትና ለብሔራዊ ማንነት ለምንለው ጉዳይ ጉልህ ሚና አለው። አንድ የትግራይ ተወላጅና አንድ የኦሮሞ ተወላጅ በአንድ ዮኒቨርሲቲ ውስጥ በአንድ ዶርሚተሪ ውስጥ ሲኖሩ በምን ያህል የመተማመን ደረጃ ይኖራሉ? የሚለውን ማጥናት ጠቃሚ ነው። ይህን በተመለከተ በአሃዝ የተጠና ጥናት ማግኘት አልቻልኩም። ይሁን እንጂ በአንዳንዶች ዘንድ የሚታየው ጽንፈኝነትና ወገንተኝነት ይህንን ሀብታችንን እንዳያተንብንና ልብ ከልብ እንዳያራርቀን ዜጎች ሃላፊነት ወስደው ሊያስብቡት ይገባል። ባህላዊ ቡድኖች ወይም ብሔሮች በባህል ልዩነቶቻቸውና በቋንቋ ልዩነቶቻቸው መቼም አይጋጩም። እንደዚህ የተጋጩ ቡድኖች አይኖሩም። የአኙዋክ ብሔርና የኑየር ብሔር አባላት ወይም የጉጂና የቡርጂ ብሔረሰብ አባላት ያንተ ምግብ አይጣፍጥም የኔ ይጣፍጣል፣ ያንተ አለባበስ አያምርም የእኔ ያምራል፣ ያንተ ዳንስ አያምርም የእኔ ያምራል፣ ያንተ ቋንቋ አይገልጽም የእኔ ይገልጻል በሚል ጦርነት አይገቡም። የባህልና የቋንቋ ልዩነት በቡድኖች መካከል ያለን መታመን አያተነውም። ብዙ ጊዜ ቡድኖች ግጭት ውስጥ የሚገቡት ይህ ባህላዊ ስብእናቸው የፖለቲካ ጥብቆ ሲለብስ ነው። ፖለቲካው የሚፈጥረው የቡድነኝነት ስሜት ልዩነትን እያራገበ ሲሄድ በአስተዳደር ጉዳይ በተፈጥሮ ሀብት ጉዳይ ግጭት ውስጥ ይገባሉ። ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ዘመናዊ ፖለቲካ የምታራምድ ሳይሆን ባህላዊ ፖለቲከኛ በመሆኗ ለቡድኖች ግጭት የተጋለጠች ከመሆኗም በላይ በቡድኖች መካከል የሚኖርን መታመን የሚያተን ከፍተኛ የፖለቲካ ሙቀት ስላለ ዜጎች ይህንን እንደተለመደው በሆነ ቴክኒክ መዋጋት አለባቸው።
እንደው ለአንባቢዎች ትንሽ ግንዛቤ ለመስጠት ያህል መታመን በተለያዩ ማኅበራዊ አውዶች ውስጥ ሲታይ በሦስት ሊከፈል እንደሚችል ባለፈው ጊዜ ስለማኅበራዊ ካፒታል ሳጠና ተረድቻለሁ። እነዚህ ሦስት የመተማመን አይነቶች የሚከተሉት ናቸው። አንደኛው የመታመን አይነት ህሊናዊ (Conscience Trust) ይባላል። በዚህ ጎራ የሚመደቡ ሰዎች የእምነታቸው መሰረት ህሊና ነው። በቡድናቸው ውስጥ ልዕልና እንዲያገኝ የሚፈልጉት ህሊናን ነው። የቡድኑ አባላት ለህሊና ከሰሩ ጤናማ የሆነ ግንኙነት ይኖራል ቡድኑም ትርፋማ ይሆናል ሩቅ ይሄዳል ብለው ያምናሉ። እነዚህ ወገኖች ህሊና ዋና የስጋት አሰውጋጅ (risk taker) አድርገው የሚያዩ ናቸው። በቡድናቸው መሃል ይሄን ያህል የጠነከረ ሲስተም ላይኖር ይችላል። ግን በፋይናንስ ጉዳይም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ህሊናን እያበረታቱ የቡድናቸውን ሕይወት በጤና ሊመሩ ይሻሉ። ሁለተኛው አይነት ደግሞ ኃይማኖታዊ መታመን ይባላል። የዚህ አይነት የቡድን አባላት ደግሞ የመታመናቸው መሰረቱ የሚጣለው በቅዱሳት መጽሐፋቸው ትእዛዝ ላይ ነው።
ቡድኖች ሲሰባሰቡ የጠራ የስራ ክፍፍል፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ ኦዲት፣ ከፍ ያለ የአባላት ተሳትፎ፣ ተጠያቂነት በጣም ይሻሉ። የእምነታቸው መሰረት የሚጣለው በነዚህ ጉዳዮች ጥራት ልክ ነው። እንተማመን እያሉ ቢሰብኳቸው ምንም አይዋጥላቸውም። ዋና ሪስክ ወሳጅ (risk taker) የሚሰራ ሲስተም በመሆኑ መሃል ላይ የሚፈልጉት ነገር ይህንን ነው። ይህንን ክፍፍል ይዘን ወደ ከፍተኛው የሰው ልጆች ስብስብ ወይም ሀገር ስንመጣ ደግሞ ህዝብ በአያሌው ሲስተሚክ ሆኖ እናያለን። ይህ ማለት ህሊናዊ መታመንን ሙሉ በሙሉ ይጥላል ማለት አይደለም። ነገር ግን በጅጉ ሕይወት ያለውን ሲስተም የሚደገፍ ሆኖ እናያለን። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በዘውዳዊ አገዛዞች ዘመን በንጉሱና በህዝቡ መካከል የሚኖረው የመታመን ድልድይ በአብዛኛው ኃይማኖታዊ ነበር። ከአምላክ የተሰጠ በመሆኑ ህዝቡ ስለተሰበሰበው ታክስ አይጠይቅም። ልምረጥ አይልም። ዝም ብሎ አምኖ ይኖር ነበር። ዘመናዊነት ሲመጣ የሰው ልጅ በእውቀቱ ሲያድግ ደግሞ ወደ ሲስተም ትረስት ነው የመጣውና ያዘነበለው። በመንግሥትና በህዝብ መካከል የሚኖረው ግንኙነት በግልጽነት፣ በኦዲት፣ በተጠያቂነት፣ በምርጫ፣ በፈቃድ ላይ የተመሰረት እንዲሆን ህዝብ ይፈልጋል። ዴሞክራሲም ይህንን ወቅታዊ የሰው ልጆች ፍላጎት ለማሟላት የቆመ ካህን ነው። ዲክተተርስ የሚባሉት የዴሞክራሲን ልብስ ለብሰው ግን ደግሞ እንደ ንጉስ የሚኖሩት ዘመኑ የሲስተም ትረስት ዘመን ስለሆነ በዴሞክራሲ ስም ለመነገድ ነው። ይሁን እንጂ ህዝብ ደግሞ እውነተኛውን እምነቱን የሚጥለው የጸዳ ሲስተም ሲፈጠርና
የተፈጠረው ሲስተም ግልጽነት፣ ተጠያቂነትን፣ የሕግ የበላይነትን ማንሸራሸር ሲችል ብቻ ነው።
በዚህ ዘመን መንግሥታት ህዝቡን ዝም ብላችሁ እመኑኝ ማለት አይችሉም። የህዝብ ሉዓላዊነትን መቀበል አለባቸው። በመሃል የተሻለ ሲስተም ማምጣት አለባቸው። ህዝብ በመንግሥት በኩል ሚስጥረኝነት መኖሩ ሲሸተው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ፣ የሕግ የበላይነት ሲጠፋ፣ መንግሥት ራሱ የማይጠየቅ ሲሆን ቀጥሎ የሚመጣው ነገር የመታመን መትነን አይደለም? መታመን ከህዝብና ከመንግሥት መሃል ብድግ ብሎ ይተናል። ስለዚህ ነው መንግሥታት አስር ጊዜ ስለግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጥሩ የሚታዩት። የኢትዮጵያን ሁኔታ ስናይ አንዱ ለቀጥታ መታመን መትነን ምክንያት የሆነው ይሄው ነው። ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ የሕግ የበላይነት ስለሌሉ እነሆ ዛሬ መታመን ተንኖ አልቆብናል። በአጠቃላይ በአሁኑ ሰዓት በሃገራችን ያለው በመንግሥትና በህዝብ መካከል ያለው መታመን በቀላሉ ሊመለስ የማይችል በመሆኑ ሀገሪቱ ቶሎ ብላ ወደ ለውጥ መሄድ አለባት። ወደ ሽግግር መግባትና የህዝብን እምነት የያዘ ሌላ መንግሥት ማቆም ያስፈልጋል።
መተማመን ሁለት ዓይነት ትርጉም ሊኖረው ሲችል አንዱ ከግብረገብ (Moral) አንጻር ያለው መተማመን ነው። በአብዛኛው በስብከት ልንገነባው የሚገባ የሞራል እሴት ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ያለው ግን ሳይንሳዊና በሚገባ ሊለካ የሚችል ነው። በዚህ አቅጣጫ መተማመን ሁለት ዋና ዋና ተለዋዋጮች(variables) አሉት። እነዚህም ዋስትና እና ስጋት ይባላሉ። በእንግሊዘኛው gurantees and risks ማለት ነው። መታመን የነዚህ የሁለት ተለዋዋጮች ስሪት ነው። በአጭር ቃል መታመንን መገንባት ማለት ዋስታናን ማስፋትና ስጋትን መቀነስ ማለት ነው። መንግሥት ዋስትናዎችን እያሰፋ ሲሄድ ስጋቶችን እየቀነሰ ሲሄድ ነው ህዝብ የሚደገፈው። በማንግስትና በህዝብ መካከል የሚኖረው የመተማመን ልክ የሚለካውም መንግሥት ባሰፋው ዋትና ልክ ነው ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ዜጎች መንግሥታቸውን ይደገፋሉ። ይህ ካልሆነና ስጋቶች እየጨመሩ ሲሄዱ በመንግሥታቸው ላይ ያለው መደገፍ ይቆምና ቶሎ ለውጥ ይፈልጉና ያምጻሉ። መንግሥት በሥልጣን ለመቆየት የሚለው ነገር እመኑኝ መልካም አስተዳደርን ተወያይተን እናመጣለን፣ ትንሽ ጊዜ ስጡን ነው። ይሄ ደግሞ ለህዝቡ ዋስትና አይሆንም። ሩብ ምእተ ዓመት ሙሉ ሥልጣን ላይ ሆኖ በጥንድ ቁጥር አደግን እያለ ሲል የነበረ መንግሥት አሁን በገጠሩ ከአስር ሚሊዮን በላይ በከተማውም እንደዚሁ ወደ አስር ሚሊዮን ህዝብ ለረሃብ ተጋልጧል። ይህ አንዱ የመንግሥትን እምነት ያተነነ ክስተት ነው። ትናንትና መቶ ፐርሰንት አሸነፍን ያለ መንግሥት ስድስት ወር ሳይሞላው ብዙ ቁጥር ያለው የኦሮሞ ህዝብ ሜዳ ላይ ወጣ። በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ተቃውሞ ነው። መንግሥት ይህንን ሲያይ መሸነፍ አይወድምና የኔ የስራ ውጤት ነው ጠያቂ ማኅበረሰብ አፈራሁ ይላል። በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ የተነሳው ህዝባዊ ንቅናቄ ኃይለሥላሴ ያፈሩት ጠያቂ ማኅበረሰብ ነበር ማለት ነው? እሳቸው ይህን ሳያውቁ ነው ያለፉት። በደል የበዛበት ህዝብ አንድ ቀን በቁጣ ገንፍሎ መውጣቱ ተፈጥሯዊ ነው። የሆነ ነገር ሰርቶ ማሳየት ያልቻለ መንግሥት ይህንን የኔ የስራ ውጤት ነው ማለቱ ይገርማል። ህዝቡ ሰልፍ የወጣው እኔ በፈጠርኩት ዴሞክራሲ ነው ሊል አይችልም። እንዲያማ ቢሆን መንግሥት ተቃውሞውን ባዳመጠ። በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ጥይት ባላፈሰሰ።
አሁን ደግሞ የተያዘው ፈሊጥ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው የሚል ነገር ነው። እውነት ነው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። የመልካም አስተዳደር እጦት ቀለል ያለ ችግር ነው ማለት ነው? መንግሥት የሚባለው ነገር መልካም አስተዳደርን ካላመጣ ምን ይሰራል። መለወጥ ነው ያለበት። ሥርዓቱ ራሱ በሙስና መረብ የቆመ በመሆኑ በምንም አይነት ሪፎርሜሽን አይለውጠውም። የኢትዮጵያ ህዝብም ከእንግዲህ በዚህ ገዢ መንግሥት ላይ ያለችው እምነት ያለ ልክ ቀጥናለችና ለሀገር አሳቢ ወገኖች ሁሉ የሽግግር ጊዜ የሚፈጠርበትን ሁኔታ መምከር ይኖርባቸዋል። በህዝብና በመንግሥት መካከል እምነት ከተነነ በኋላ የሚጠበቅ ነገር አይኖርም። ለውጥ የግድ ሊመጣ ይገባዋል። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።
ገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.com
<< Home