Thursday, February 16, 2012

Waldeba's monastic life under threat

የዋልድባ ገዳማት ህልውና እና ክብር ለአደጋ ተጋልጧል
የካቲት 1 ቀን 2ሺህ 4 ዓ.ም









በገዳሙ ክልል እና ዙሪያ (በዓዲ አርቃይ ወረዳ በኩል) የፓርክ ይዞታ ለመከለል እና
የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም በሚል በሚካሄደው የጥርጊያ መንገድ ሥራ (ከማይ ፀብሪ
እስከ ዕጣኖ ማርያም) የቅዱሳን አበው ዐፅም እየፈለሰ መሬቱ እየታረሰ ነው።
· የሦስቱ ገዳማት ማኅበረ መነኮሳት ዕቅዱ የገዳሙን ክብር የሚጋፋ ህልውናውንም
የሚያጠፋ በመሆኑ እንዲቆምላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።

· መንግሥት ካቀዳቸው 10 ግዙፍ የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክቶች አንዱ በዋልድባ
ገዳም ክልል እና ዙሪያ (ወልቃይት - መዘጋ) የሚቋቋም ሲሆን በዛሬማ ወንዝ ላይ 3.8
ቢልዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያለውና 40,000 ሄ/ር የሸንኮራ ተክል
የሚለማበት ግድብ ይቆምለታል፤ ግድቡ በሚሸፍነው ስፍራ (ማይ ዲማ) የሚገኙ አራት
አብያተ ክርስቲያን የሚነሡ ሲሆን ለ10,000 የፕሮጀክቱ ጊዜያዊ እና ቋሚ ሠራተኞች
የመኖሪያ ካምፕ ግንባታ እየተካሄደ ነው።
· “በቅድስት ገዳማችን ዋልድባ ውስጥ ለሚደረገው አግባብ ያልሆነ እንቅስቃሴ አበው
ቅዱሳን አባቶቻችን ልዩ ሥራ እንዳይሠራባት የውግዘት ቃል (እንበለ ፈላሲ ኢይባዕ
ነጋሲ) ያሳለፉባት ቦታ በመሆኗ ማኅበረ መነኮሳቱ ባደረግነው ምልአተ ጉባኤ መሠረት
ለሚሠራው ሥራ ፈጽሞ ፈቃዳችን አለመሆኑንና የአባቶቻችን ቅዱሳንን ፈለግ ሕግና
ሥርዐት ተከትለን የምንሄድ መሆናችንን በጥብቅ እናሳውቃለን”።

(ደጀ ሰላም፤ ፤ ፌብሩዋሪ 10/2012)፦

2
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ እና ታሪካዊ ገዳማት አንዱ ነው፤
ለግሑሳን(ፍጹማን) ባሕታውያን መሸሸጊያ፣ ለስውራን ቅዱሳን መናኸርያ፣ በብዙ ሺሕ
ለሚቆጠሩ መነኮሳት፣ መነኮሳይያት እና መናንያን መጠጊያ፣ ለምእመናኑንም መማፀኛ እና
ተስፋ ነው - የዋልድባ ገዳም፡፡


ቅዱሳን አበው እንደ ጽፍቀተ ሮማን የሰፈሩበት፣ እንደ ምንጭ የሚፈልቁበት ገዳሙ
እመቤታችን ከልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ስደት ወቅት በኪደቱ
እግር ከረገጧቸው መካናት አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ ጌታችን የወይራ ተክል ተክሎና አለምልሞ
አርኣያ ስቅለቱን ገልጾበታል፤ ለቅዱሳኑ “እንደ ኢየሩሳሌም ትኹንላችሁ፤” ብሎ ቃል
ኪዳን በመስጠት እህል እንዳይዘራባት፣ ኀጢአት እንዳይሻገርባት፣ ከድንግል አፈሯ
የተቀበረ እንዳይወቀስባት እንዳይከሰስባት አዝዟል፡፡ በሰሜን ተራራዎች ግርጌ ዙሪያዋን
በሰሜን አንሴሞ፣ በምሥራቅ ተከዜ፣ በምዕራብ ዘወረግ እና በደቡብ ዜዋ በተባሉ አራት
ወንዞች በተከበበችውና የኢትዮጵያ ገዳማት ሁሉ መመኪያ በተባለችው ገዳም ከሙዝ
ተክል ከሚዘጋጀው ቋርፍ እና ቅጠላ ቅጠል በቀር እህል አይበላባትም፡፡
በዚያ ቅዱሳን አበው፣ መነኮሳት እና መነኮሳይያት ረሀቡንና ጥሙን ታግሠው፣
የአገርን ቅርስና ሀብት ጠብቀው ለኢትዮጵያና ለመላው ዓለም እያለቀሱና እየጸለዩ፣ ዲማ
በተባለው ፍልፍል ዛፍ በኣታቸው እያለፉ ኖረዋል፤ ቦታው ከፍተኛ የድኅነትና ሃይማኖት
ሥፍራ ነውና ዛሬም ለአገር ሰላም፣ ፍቅርና ዕድገት ያልተቋረጠ ጸሎት እየተካሄደበት
የሚገኝበት ቢሆንም ለ2000 ዓመታት በነገሥታቱ ሳይቀር ተጠብቆ የኖረውን ክብሩንና
ሞጎሱን የሚፈታተን፣ ገዳማዊ ሕጉንና ሥርዐቱን የሚጋፋ፣ ማኅበረ መነኮሳቱንም ለከባድ
ኀዘንና ጭንቀት የሚዳርግ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡
3

የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ዘቤተ ሚናስ ማኅበር፣ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት
ገዳም ማኅበር እና የዋልድባ ዳልሽሓ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ማኅበር ምልአተ
ጉባኤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መለስ ዜናዊ በጻፉት አምስት ገጽ ደብዳቤ ላይ
እንደተገለጸው÷ በዓዲ አርቃይ ወረዳ በኩል የዋልድባን ገዳም ውስጡን በፓርክነት
ለመከለል በቀለም የተቀለሙ ምልክቶች እየተተደረጉ ነው፡፡ በወልቃይት ወረዳ ልዩ ስሙ
መዘጋ በተባለ የገዳሙ የእርሻ እና አዝመራ ቦታ ላይ መንግሥት የዛሬማን ወንዝ ገድቦ
የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በገዳሙ ክልል ዘልቆ የሚያልፍ
ጥርጊያ መንገድ ለመሥራት በግሬደር እና ሌሎችም ከባድ የሥራ መሣሪያዎች
በሚካሄደው ቁፋሮ የቅዱሳን አባቶች ዐፅም እየታረሰና እየፈለሰ መሆኑ የገዳሙን
መነኮሳትና መናንያን ከፍተኛ ሐዘንና ጭንቀት ላይ ጥሏቸዋል፡፡
የማኅበረ መነኮሳቱ ደብዳቤ ጨምሮ እንደሚያብራራው የዛሬማ ወንዝ ግድብ
ሲቆም በውኃ ሙላቱ ሳቢያ ከሚጠፉት የገዳሙ ወሳኝ ይዞታዎች መካከል የሚከተሉት
ይገኙበታል፡-
1) ልዩ ስሙ አባ ነፃ የተባለ የብዙ ቅዱሳን ዐፅም በክብር የፈለሰበትና የረገፈበት፣
ብዙ መነኮሳት እና መናንያን የሚቀመጡበት (የሕርመት/ተዐቅቦ ቦታ) የጻድቁ አቡነ
ተስፋ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንና መቃብር እንዲሁም የሙዝ ቋርፍ በከፍተኛ ደረጃ
የሚዘጋጅበት እጅግ ሰፊ የሆነ የአትክልት ሥፍራ፤
2) በመዘጋ የሚገኙት ሞፈር ቤቶች/በገዳሙ ውስጥ እህል ስለማይበላ የዓመት
ቀለብ የሆነ ቋርፍ የሚዘጋጅበት የአትክልት ስፍራ/፤
3) በመዘጋ የገዳሙ መነኮሳት እህል የሚቀምሱበት ቤት፤
4) ጥንታውያን የሴቶች መነኮሳይያት መኖሪያ ገዳሞችና ታሪካዊ ቦታዎች፤

እነዚህም፡-
4.1) ማየ ሕርገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከመነኮሳት፣
መነኮሳይያት፣ መናንያን፣ የገዳሙ ተማሪ ቤቶችና መኖሪያ ቤቶቻቸው፤
4
4.2) ዕጣኖ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የመነኮሳት፣ መነኮሳይያት
አጠቃላይ መናንያን የገዳሙ የቤተ ክህነት ትምህርት መማሪያ ቤቶች ከመምህሮቻቸውና
ተማሪዎቻቸው ጋራ፤
4.3) በተለይም በዋልድባ አብረንታንት ውስጥ ያሉ ባሕታውያን፣ መነኮሳትና
መናንያን የሙዝ ቋርፍ የሚዘጋጅበት ገዳሙ በዋናነት የሚተዳደርበት እጅግ ሰፊ
የአትክልት ቦታ፤
4.4) ደላስ ቆቃህ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን የመነኮሳት፣ መነኮሳይያት፣
መናንያን መኖርያ ቤቶች፣ የገዳሙ ቤተ ክህነት ት/ቤቶች፣ መምህሮቻቸውና
ተማሪዎቻቸው እስከ መኖርያ ቤቶቻቸው ናቸው፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት የገዳሙ ይዞታዎች ከጠፉ ገዳሙ ምንም ዐይነት የገቢ ምንጭና
መተዳደር /በደላሳ ቆቃህ እንደ ማሽላ፣ ዳጉሳ በማምረት/ የማይኖረው በመሆኑ መነኮሳቱ፣
መነኮሳይያቱ፣ መናንያኑ፣ መምህራኑና ተማሪዎቻቸው ለረሃብ እና ስደት የሚዳረጉ
በመሆኑ ማኅበሩ ሙሉ በሙሉ እንደሚያከትምለት ያስረዳው ደብዳቤው÷ መንግሥት
ሐዘናቸውንና ጩኸታቸውን ሰምቶ የገዳማቸውን ሕግ እና ሥርዐት እንዲያስከብርላቸው
ተማፅነዋል፡፡



ቀደም ሲል በተለይም ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ማይ ሰርኪን ከተባለው ቦታ ወርቅ
እናወጣለን በሚሉ ቆፋሪዎችና ዕጣን እንለቅማለን በሚሉ መቀርተኞች (ቁጥራቸው
በዐሥር ሺሕዎች በሚገመት ሰፋሪዎች) ተጥለቅልቀው ሲታወኩና ሲረበሹ መቆየታቸውን
የጠቀሰው የማኅበረ መነኮሳቱ ደብዳቤ አሁን ደግሞ ፓርክ ለመከለል፣ የስኳር ፋብሪካ
ለማቋቋምና ጥርጊያ መንገድ ለማውጣት የሚካሄደው እንቅስቃሴ ለገዳሙ ህልውና
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነበት አትቷል፡፡
በበጋ ወቅት መንሥኤው የማይታወቅ የሰደድ እሳት ከሚያወድመው ደን ባሻገር
በወርቅ ጫሪዎቹ እና በዕጣን መቀርተኞቹ ሳቢያ አበው መነኮሳት ጭብጥ ቋርፍ ይዘው
ሱባኤ የሚይዙባቸው/የሚሰወሩባቸው ዛፎች (ፍልፍል ዲማ)፣ መድኃኒትነት ያላቸው

ዕፀዋትና የግሑሳኑ መሳፈርያ የሆኑት የዱር እንስሳት (አንበሳ፣ አጋዘን፣ ነምር) ከገዳሙ
እየጠፉ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡
ከማኅበረ መነኮሳቱ ጋራ ባለፈው ዓመት የመዘጋ እና የወልቃይት ነዋሪዎች ማይ ገባ
ንኡስ ወረዳ ላይ የተቃውሞ ድምፃቸውን በሰልፍ ማሰማታቸውንም ያወሱት የገዳማቱ
ተወካዮች ልማትን የሚቃወሙ ባይሆንም ስለ ዕቅዱ ምንም የተገለጸላቸው ነገር ባለመኖሩ
ቦታው የጸሎት፣ የተጋድሎና የቅድስና መሆኑ ቀርቶ የዓለማውያን መናኸርያ፣ የነጋድያንና
የሕዝብ መስፈርያ፣ የመኪና መሽከርከርያ እንዲሆን ፈቃደኞች እንዳይደሉ የገዳሙ
ማኅበር አባላት ገልጸዋል፤ በገዳሙ ልዩ ሥራ እንዳይሠራ “እንበለ ፈላሲ ኢይባዕ ነጋሲ”
በማለት ቀደምት አባቶቻቸው ያስተላለፉትን የውግዘት ቃል በማስጠበቅ በቅዱሳኑ ፈለግ
ሕግና ሥርዐት መጓዛቸውን እንደሚቀጥሉም በጥብቅ አስተውቀዋል፡፡
በአምስት ዓመቱ የመንግሥት ልማት እና ትራንፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት በስኳር
ምርት ራስን ለመቻል ከሚቋቋሙት ዐሥር ግዙፍ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች መካከል
አንዱ የ4.2 ቢልዮን ብር ዕቅድ የተያዘለት ይኸው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ነው፡፡
ፋብሪካው በ40,000 ሄ/ር ላይ የሚለማውን የሸንኮራ ተክል የሚጠቀም ሲሆን የውኃ
ምንጩም በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚሠራው ርዝመቱ 700 ሜትር፣ ከፍታው 138 ሜትር
የሆነና 3.8 ቢልዮን ሜትር ኪቢዩክ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ግድብ ነው፡፡
ውኃው ያርፍበታል በተባለው ማይ ዲማ በተባለው ቦታ የሚገኙት የማር ገጽ ቅዱስ
ጊዮርጊስ፣ የማይ ገባ ቅዱስ ሚካኤል፣ የዕጣኖ ቅድስት ማርያም እና የደለሳ ቆቃህ አቡነ
አረጋዊ አብያተ ክርስቲያን እንደሚነሡ ተነግሯል፡፡ ሥራውን ያካሂዳል የተባለው
የፌዴራል ውኃ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለ10,000 የፕሮጀክቱ ቋሚ
እና ጊዜያዊ ሠራተኞች የካምፕ ግንባታ እየተከናወነ፣ ቦታውንም ምቹ የማድረግ ሥራ
እየተሠራ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
በሰሜን ምዕራብ ትግራይ - ሽሬ እንዳሥላሴ እና በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ዓዲ
አርቃይ ወረዳ ክልል በሚገኙት ሦስቱ የዋልድባ ገዳማት በአጠቃላይ ከ3000 ያላነሱ
መነኮሳትና መነኮሳይያት የሚገኙ ሲሆኑ የሴቶች ገዳም በሆነው የዳልሽሓ ኪዳነ ምሕረት
አንድነት ገዳም ከ1500 ያላነሱ ሴት መነኮሳይያት ይገኙበታል፡፡ የዋልድባ አብረንታንት
ገዳም ምክሆን ለገዳማተ ኢትዮጵያ ማኅበር ዘቤተ ሚናስ ዋነኛው የሕርመት/ተዐቅቦ ቦታ
ሲሆን ወንዶች መነኮሳት ብቻ ያሉበት፣ እስከ 50 ዓመት ድረስ በአርምሞ ከሰው
ተነጋግረው የማያውቁ ቅዱሳን በዘመናችን ሳይቀር የሚገኙበት ነው፡፡
ገዳሙን በማደራጀት እና የተባሕትዎን ኑሮ በማጠናከር በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን
ከነበሩትና ሰባቱ ከዋክብት ከሚባሉት የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዛሙርት አንዱ
ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል (ሳሙኤል ፀሐይ ዘዋሊ) ይጠቀሳሉ፤ ገዳሙን ያቀኑትም በዐምደ
ጽዮን ዘመነ መንግሥት በ1319 ዓ.ም ነው፡፡ የገዳሙን ኑሮ መልክ የሰጡት ከደብረ

ሊባኖስ በሄዱት እንደ አባ ሙሴ የመሳሰሉት አባቶች ሲሆኑ “በገዳም እንኖራለን፤ እህል
አይገባንም” በማለት ከእርሳቸው ጊዜ ጀምሮ የመነኮሳቱ ምግብ ቋርፍ - ሙዝ በጨው
ተቀቅሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
የዋልድባ መነኮሳት ከነገሥታት ጉልት አይቀበሉም ነበር፤ ሲሰጥም አጥብቀው
ይቃወሙ ነበር፡፡ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ /1426 - 1460 ዓ.ም/ ዘመነ መንግሥት የዋልድባ
ገዳም በአራቱ ጅረቶች መካከል እንዲሆን ተከልሎ ገዢ እንዳይገባ፣ አራሽ እንዳይሠማራ
ተከልክሏል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን